“ምን ይፈጠር ይሆን? እያልን በስጋት እየጠበቅን ነው” በቱርክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቱርክ እና በሶሪያ ድንበር አካባቢ ዕሁድ ለሰኞ ሌሊት ላይ በተከሰተው ከባድ ርዕደ መሬት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
የነፍስ አድን ሠራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ፈልጎ የማውጣት ሥራ እያከናወኑ ነው።
የአደጋው ሰለባዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልም ተሰግቷል።
ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የረጅም ዘመን ግንኙነት ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለንግድ፣ ሥራ፣ ህክምና፣ ለትምህርት እንዲሁም ለመዝናናት የሚጓዙባት በአውሮፓ እና በአስያ አህጉር መካከል የምትገኝ አገር ናት።
ስለዚህም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ውስጥ ይገኛሉ፤ በተለይ ይህ ተፈጥሯዊ አደጋ ባጋጠመበት ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን የዘመድ ጓደኞቻቸው ደህንነት ስጋት ፈጥሮባቸዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ያሉትም ኢትዮጵያውያን ከባዱ የመሬት መንቀጥቀጥ በፈጠረው አደጋና ስጋት ውስጥ እንዴት እንደሆኑ ለማወቅ ቢቢሲ የተወሰኑትን ለማግኘት ሞክሯል።
ለቱርክ መንግሥት ዜና ወኪል፣ አናዶሉ የሚሰራው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ሳዲቅ ከድር፣ በአገሪቱ ውስጥ በቆየባቸው ስምንት ዓመታት እንዲህ ዓይነት አደጋ አጋጥሞ እንደማያውቅ ይናገራል።
ሳዲቅ እንደሚለው የመጀመሪያው ርዕደ መሬት የተከሰተው ከሌሊቱ 10፡17 አካባቢ ሲሆን፣ እንደ ቱርክ የድንገተኛ አደጋዎች ሚኒስቴር መረጃ በሬክተር ስኬል 7.7 የተለካ ነውጥ ነበር የተከሰተው።
ከሰዓታት በኋላ በቱርክ ደቡባዊ ምሥራቅ ከተማ ካህራማናማራስን ማዕከል ያደረገ በ7.6 ሬክተር ስኬል የተለካ ሌላ ርዕደ መሬትም ተከስቷል።
እንደ ሳዲቅ ከሆነ የርዕደ መሬቱ ንቅናቄ ርቀው እስከሚገኙት አንካራ የመሳሰሉ ቦታዎች የተሰማ ነበር።
“እኛ ራሱ ከሕንጻችን ወርደን ነው ያሳለፍነው” ይላል የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ።
ከአደጋው በኋላ የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞች የነፍስ አድን ሥራ ለማከናወን የተሰማሩ ሲሆን፣ የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴርም በአየር እርዳታ እያደረገ ነው።
ሳዲቅ፣ወደ 45 የሚጠጉ ሌሎች አገራትም እርዳታ ለማቅረብ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
“ያልፈረሱ ሕንጻዎች ተነቃንቀዋል፤ ሊፈርሱ የደረሱም አሉ”
የመጀመሪያው ርዕደ መሬት የተከሰተው ከቱርክ ዋና መዲና ኢስታንቡል በ850 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ጋዚያንቴፕ ግዛት ውስጥ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገረው እና በዚህ ግዛት በሚገኘው ጋዚያንቴፕ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ፣ እርሱ ባለበት ከተማ ብዙ ፎቆች እንደፈረሱ እና በርካታ ሰዎች እንደሞቱ ተናግሯል።
ርዕደ መሬቱ ዕሁድ ሌሊት እንዳጋጠመ የሚናገረው ተማሪው፣ ከዚያ ሰዓት በኋላ “የውጪው ቅዝቃዜ የሚቻል ባይሆንም ነዋሪው ደጅ ላይ ፈሶ ነው የሚገኘው” ይላል።
ተማሪው እንደሚለው ርዕደ መሬቱ ያጋጠመው ሁለት ጊዜ በመሆኑ ያልፈረሱ ሕንጻዎችም ተነቃንቀዋል። ሊፈርሱ የደረሱም አሉ።
ደኅንነታቸው እስከሚረጋገጥ ድረስም ነዋሪው ወደ ሕንጻዎቹ እንዳይገባ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።
አሁን ላይ ከቤቱ ውጪ ለሚገኘው ሕዝብ ጊዜያዊ የማደሪያ ድንኳን እየተዘጋጀ መሆኑን ተማሪው ለቢቢሲ ገልጿል።
አደጋው ከመከሰቱ በፊት የተሰጠ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልነበር የሚገልጸው ተማሪው፤ አደጋው በድንገት ሰው በተኛበት ሰዓት በማጋጠሙ የከፋ ጉዳት እንዳስከተለ ይናገራል።
“እኛ አካባቢ የፈረሰ ፎቅ ባይኖርም በኦንላይን የምናያቸው ነገሮች የሚረብሹ ናቸው” ይላል።
ይኸው ተማሪ፣ እስካሁን ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊ ተማሪ አለመኖሩንና አንካራ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋርም መረጃ መለዋወጣቸውን አክሏል።
በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አደም መሐመድ ማህሙድ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በደቡባዊ ቱርክ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡት ሐዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የተጎዱትም እንዲያገግሙ ተመኝተዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
“ነዋሪዎች ከአሁን አሁን ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል በስጋት እየተጠባበቁ ነው”
የአናዶሉ ጋዜጠኛው ሳዲቅ፣ አደጋው ወደ ተከሰተበት ሥፍራ ባያመራም፣ ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ከፍርስራሽ ውስጥ ለማውጣት የሚደረጉ ጥረቶችን በጣቢያው ከሥፍራው በቀጥታ ከሚተላለፈው ሥርጭት መመልከቱንም ይናገራል።
ሳዲቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጡ ለተወሰኑ ቀናት በአነስተኛ መጠን ሊቀጥል ይችላል ተብሎም እንደሚጠበቅ መረጃዎች መኖራቸውን አመልክቷል።
በዚህም ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤት ውጪ እንዲሆኑ እና ያልፈረሱ ሕንጻዎች ለደኅንነት ሲባል ባዶ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ሳዲቅ እስካሁን ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ እንደተናገረው በአደጋው በቱርክ በኩል 1014 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 2000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
ጨምሮም “ጭንቀቱ አሁንም እንዳለ ነው። ነዋሪዎች ‘ከአሁን አሁን ምን ሊፈጠር ይችላል?’ በሚል በስጋት እየተጠባበቁ ነው።”
ሳዲቅ እስካሁን በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ መረጃ ባይኖረውም፣ በአካባቢው ትምህርታቸውን ከሚከታተሉ ተማሪዎች ውስጥ ግን የተጎዳ ተማሪ የለም ብሏል።
ኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች በቱርክ ከሚገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃደኝነት ወደ ቦታው በመሄድ ድጋፍ ለማድረግ እየሞከሩ መሆናቸውንም ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY VIA GETTY IMAGES
ቱርክ እና ሶሪያ በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ በተከሰተ ከባድ ርዕደ መሬት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ ሁለት ሺህ መጠጋቱን ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ዛሬ ጠዋት በተከሰተው ርዕደ መሬት በቱርክ እስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ በሶሪያ ደግሞ ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል።
አደጋ ያጋጠመው ቱርክ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንበት ደቡብ ምሥራቋ ጋዚያንቴፕ ግዛት ውስጥ ነው።
የቱክር ፕሬዝዳንት ረሲፕ ኤርዶዋን ይፋ እንዳደረጉት በአገራቸው ግዛት ውስጥ ብቻ ቢያንስ 912 ሰዎች በአደጋው ሲሞቱ፣ 5ሺህ 383 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኤርዶዋን ጨምረውም በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ለመገመት አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፍለጋ ሥራው ተጠናክሮ ሲቀጥል የሰለባዎች ቁጥር ይጨምራል ብለዋል።
በአጎራባች ሶሪያ ውስጥ በርዕደ መሬቱ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች አሃዝ 783 መድረሱን የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።
ርዕደ ሬቱ በመታቸው አካባቢዎች ያሉ ሕንጻዎች የፈራረሱ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም በተደረመሱት ሕንጻዎች ውስጥ ተቀብረው መውጣት እንዳልችሉ ተገልጿል።
ይህም በሰዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በትክክል ማወቅ እንዳይቻል አድርጓል ተብሏል።












